ቀጥታ፡

”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አካል የሆነ ክልል አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር በሀዋሳ ከተማ ተከፈተ

ሀዋሳ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ)፡- ”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ አካል የሆነ ክልል አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኢግዚቢሽንና ባዛር በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ተከፈተ።

"የኢንዱስትሪዎቻችን ምርታማነት ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ የተከፈተው ኤግዚቢሽንና በዛር እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል።


 

የሲዳማ ክልልና የፌዴራል ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በተከፈተው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከ100 የሚበልጡ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ኢንዱስትሪዎቹ በቆዳ ውጤቶች፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በአልባሳት እንዲሁም በግብርናና ሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው።


 

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል ሲሆን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዚህ ንቅናቄ መሠረት ያመረቱ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን የሚያቀርቡበት ነው ተብሏል።

በመርሀ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማበረታታትና ያላቸውን የገበያ ትስስር የማስፋት ዓላማ አለው።


 

በመክፈቻ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣  የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አማካሪና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አስፋው አበበ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም