ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ ንቅናቄ መርሐግብር ተጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ):- የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የወጣቶች የቦንድ ግዢ ንቅናቄ መርሐ-ግብር ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።


 

በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ በአዲስ አበባ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ፣ የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት መለስ አባተ እና ወጣቶች ተገኝተዋል።

በቦንድ ግዢ ንቅናቄው ከወጣቱ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱን ወጣት መለስ ገልጿል።


 

የአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ወጣቶቹ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ወጣቶች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ወጣቶች በማህበራዊና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ፍሬያማ መሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የቦንድ ግዢ መርሐ-ግብሩ “እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም