ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2015(ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ባህር ዳር ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ባህር ዳር ከተማ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አርባ ምንጭ ከተማ በ22 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።

ባህር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማ በበኩሉ ካለፉት የአምስት የሊግ ጨዋታዎች አንዱን በማሸነፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እስኪያደርግ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ22ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 30 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

አዳማ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሐ-ግብር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ለገጣፎ ለገዳዲን 2 ለ 0 እንዲሁም ፋሲል ከነማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 ማሸነፋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም