ቀጥታ፡

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በኅብረተሰቡ ወስጥ ሽብርና ፍርሃትን በመፍጠር እኩይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴና ድርጊት እያመከነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23/2015 (ኢዜአ)፦ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በኃይል ለማፍረስና እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት ከፍተኛ አመራሮችን በመግደል፣ በኅብረተሰቡ ወስጥ ሽብርና ፍርሃትን በመፍጠር እኩይ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሕገ ወጥ መንገድ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴና ድርጊት እየመከነ ነው።

በዚህም መሠረት የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባለፈው ጊዜ ከወሰዳቸው ርምጃዎች በተጨማሪ፣ በዛሬው ዕለት ጽንፈኛው ቡድን ሰሜን ወሎ ዞን ተኩለሽ ጫካ ቆፍሮ ያዘጋጀው ስቶር ውስጥ የቀበራቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾችን መያዙን የጸጥታና የደኅንነት ምንጮች ገልጠዋል።


 

ሕገ ወጡና ፅንፈኛው ኃይል ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ የቀረበለትን አማራጭ በመርገጥ፣ በጥፋት ኃይልነት ለመቀጠል ያቀደው መንገድ በጸጥታና የደኅንነት አካላት እየከሸፈበት ይገኛል።

ከሀገር ውስጥና ከውጭ በገንዘብና በፕሮፓጋንዳ ተደራጅቶ፣ የሽብር ተግባር ለመፈጸም የተመሠረተው ይህ ሕገ ወጥ ቡድን፣ አዝማቾቹና ዘማቾቹ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ይገኛሉ።


 

ለዚህ የሽብር ተግባር ያከማቿቸው የጦር መሣሪያዎችም በጸጥታ አካላት እየተያዙ ናቸው። በትናንትናው ዕለት ከተያዙት ሕገ ወጥ መሣሪያዎች በተጨማሪ በዛሬው ዕለት ከላይ የተገለጡት የተደበቁ መሣሪያዎች መገኘታቸው ተገልጧል።


 

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጽንፈኞችን ለሕግ ለማቅረብና የሽብር ተልዕኳቸውን ለማክሸፍ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጧል።

ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን የፅንፈኛችን የጥፋት ሴራ የማከሸፍ እና ለፀጥታ አካለት የሚያደረገውን የመረጃ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጸጥታ ግብረሃይሉ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም