ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ)፦ በዛምቢያ ንዶላ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

ዛሬ በሻምፒዮናው የሶስተኛ ቀን ውሎ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች በተካሄደው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል አትሌት አለምናት ዋለ አሸንፋለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬሕይወት ገሰሰ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።


 

ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ እስካሁን በሻምፒዮናው ያገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ ወደ ሶስት ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከ20 አመት በታች 1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች እና ከ20 አመት በታች 3 ሺህ ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ እስካሁን በሻምፒዮናው 3 የወርቅ፣ 6 የብር እና 3 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

ሁለተኛው የአፍሪካ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም