ቀጥታ፡

የሃላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማት በቱሪዝም ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ሁነኛ ማሳያ ነው- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ)፦ የሃላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት የአገሪቷን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በቱሪዝም ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለአገር አካል የሆነውን ሃላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፍተዋል። 


 

ሪዞርቱ የገበታ ለአገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል ሲሆን ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁ ተገልጿል።

የሪዞርቱ ግንባታ የአካባቢው ማህበረሰብን ነባር የኪነ-ሕንጻ ጥበብ ከዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ መገንባቱም ተገልጿል። 

በውስጡ ፕሬዝዳንታዊ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች እና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን የያዘ ነው።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የሃላላ ኬላ ሪዞርት የተፈጥሮ ፀጋዎችን በማልማትና በመጠቀም በኩል ለሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች አርአያ የሚሆን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።


 

የሪዞርቱ ግንባታ የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በማልማት ገጽታዋን ከመቀየር ባለፈ በቱሪዝም ሀብት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል። 

በመሆኑም ከዚህ ልምድ በመውሰድ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሀብቶችን በማልማት የሕዝብን ታሪክና ባህል አጉልቶ ለማውጣትና ሀብት ለመፍጠር መስራት ይገባል ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው።

የሃላላ ኬላ ሪዞርት ተሞክሮን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን ይገበል ብለዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በበኩላቸው የሃላላ ኬላ ሪዞርት ፕሮጀክት መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምን ለማረጋገጥ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የአገርን ገጽታ የሚያጎላና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም አክለዋል።


 

በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ልማት ስራዎችን ለማፋጠን እንደሚያግዝ አመልክተዋል። 

የሃላላ ኬላ ሪዞርት በተገነባበት ስፍራ የሚገኘው የጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅም በውሃ ላይ መዝናናት ለሚፈልጉ ጎብኝዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ መዘጋጀቱም ተመላክቷል። 


 

በተጨማሪም ቀደምት የዳውሮ ንጉስ ሃላላ ስም የተገነባው የሃላላ ድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) ታሪካዊነቱን እንደጠበቀ በስፍራው ተጨማሪ የመስህብ አካል በመሆን እንደሚያገለግል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም