በኢትዮጵያ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማስፋት ልምድና እውቀትን በመጋራት ማልማት ይገባል- የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማስፋት ልምድና እውቀትን በመጋራት ማልማት ይገባል- የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማስፋት ልምድና እውቀትን በመጋራት ማልማት እንደሚገባ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ከ200 በላይ የከተሞች ከንቲባዎች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ቢሮ፣ የአዲስ አፍሪካ ኮንቬሽን ማዕከል፣ መስቀል አደባባይና የቤተ-መንግሥት እድሳት ፕሮጀክትን የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።
የለሚ እንጀራ ማዕከል፣ ለአቅመ ደካማ የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እና ሌሎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ ከተሜነትና ብልጽግና አይቀሬ የእድገት ምሰሶ በመሆናቸው ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ከተሞችን ለማስፋትና ልማታቸውን ለማጠናከር ልምድና እውቀትን በመጋራት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የከተሞች ከንቲባዎች በመዲናዋ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የበለጸጉ አገራት ከተሞቻቸው ከግብርና ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው አንስተው፤ በኢትዮጵያም ሰፊ የከተማ ግብርና እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የከተማ ከንቲባዎችም በመዲናዋ የተሰሩ ሥራዎችን ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ጥሩ መነቃቃት የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመሯቸው ፕሮጀክቶች የተመዘገበው ውጤት የከተማ ከንቲባዎችና አመራሮች በጉብኝቱ ፕሮጀክትን ለመምራት ትምህርት የወሰዱበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀሊዲ እና የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ዚያድ አብዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመዲናዋ የተከናወኑ ሰው ተኮርና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ተመስገን አለማየሁ እና የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ባጓል ጆክም በአዲስ አበባ የተመለከቷቸው ፕሮጀክቶች ጥልቅ ተሞክሮ ያገኙባቸው መሆኑን ገልጸዋል።