በአደገኛ ዕፅ ዝውውር የተጠረጠረው ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 23/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአደገኛ ዕፅ ዝውውር የተጠረጠረውን ጋዜጠኛ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

በአደገኛ ዕፅ ዝውውር የተጠረጠረው ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው በበረራ ቁጥር ET-600 አውሮፕላን በመሳፈር ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ዕፁን ለማስተላለፍ ሲሞክር እንደሆነ ገልጿል፡፡


 

ከጉዞ በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በሚያደርገው የተለመደ የሰው አካልና የሻንጣ ፍተሻ በተጠርጣሪው የጉዞ ሻንጣ አካል ውስጥ ተሰርቶ ሊያልፍ የነበረ በዱቄት መልክ የተዘጋጀ 2 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም ኮኬይን አደገኛ ዕፅ ከተጠርጣሪው ጋዜጠኛ ጋር ትናንት ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ40 ላይ መያዙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ፖሊስ ግለሰቡ ይሰራበት ከነበረው መስሪያ ቤት ከአራት ወር በፊት በስነ-ምግባር ችግር መሰናበቱንና ከዚህ ቀደም ወደ ተለያዩ አገራት በሰዎች አማካኝነት አደገኛ ዕፅ ይልክ እንደነበር የፖሊስ የምርመራ ውጤት እንደሚያሳይ ገልጿል።

አደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ክትትል ሕብረተሰቡ የተለመደውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልና በጉዞ ወቅት ከሶስተኛ ወገን አድርሱልኝ በሚል የሚሰጡ ቁሳቁሶችንና ሻንጣዎችን ይዘት በሚገባ መለየትና የሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ማረጋገጥ እንዳለበት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም