ቀጥታ፡

በየአካባቢያችን ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን ለልማት በማዋል ሕብረ-ብሔራዊና ለሁሉም ዜጎች የምትበቃ አገር መገንባት ላይ በጋራ መሥራት አለብን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ)፦ "በየአካባቢያችን ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን ለልማት በማዋል ሕብረ- ብሔራዊና ለሁሉም ዜጎች የምትበቃ አገር መገንባት ላይ በጋራ መሥራት አለብን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለሀገር አካል የሆነውን ሃላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፍተዋል፡፡

ሪዞርቱ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል ሲሆን፤ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጥራት ተገንብቶ ተጠናቋል፡፡


 

ሪዞርቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታም የአካባቢው ማኅበረሰብ ነባር የኪነ-ህንፃ ጥበብን ከዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ ማራኪ በሆነ አግባብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

በውስጡም ፕሬዝዳንታዊ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎችና ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎችን የያዘ ነው፡፡

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ልክ አለመልማቷን ተናግረዋል፡፡


 

በመሆኑም ከመገፋፋትና ጥላቻ ወጥተን የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን በጋራ ለማልማት መሥራት አለብን ብለዋል፡፡

የሃላላ ኬላ ሪዞርት ተፈጥሮን ከማኅበረሰባዊ እሴቶች ጋር በማዋሃድ የተከናወነ ድንቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ፕሮጀክቱ የዳውሮ ንጉስ የሆኑት ንጉስ ሃላላ ያስገነቡትን የድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለቱሪዝም ልማት እንዲውል ዕድል መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡

ሪዞርቱ በተገነባበት ሥፍራ የሚገኘው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ኃይቅም የሪዞርቱ ተጨማሪ ውበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ፣ ባህልና ቅርስን አስተሳስሮ የያዘውን የሃላላ ኬላ ሪዞርት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተፈጥሮን ለልማት የሚያውሉ መሰል ሥራዎች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሰፉም ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊነት ከቋንቋ፣ ባህልና እምነት በተጨማሪ በተፈጥሮ እንደሚገለጽ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ዓይነት የአየር ፀባዮችና የተፈጥሮ ሃብቶች የኢትዮጵያ መገለጫዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የአካባቢያችንን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ያሉንን የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ለልማት ለማዋል መትጋት አለብን ነው ያሉት፡፡

የሪዞርቱ መገንባትም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ነው የተጠቆመው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም