የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/20215(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ናቸው።
በስምምነቱ መሰረት የሀዋሳ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ እንዲሁም የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማጠናከር (ስማርት ሃዋሳን ለመገንባት) በጋራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ከተሞች ለማዘመን፣ ቀልጣፋና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ኢንስቲትዩቱ የሀዋሳ ከተማን ምቹ ለማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመንና በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ መፈረሙን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዙ 20 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ዘመናዊ ካሜራዎችን ጨምሮ ሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በጸጥታ፣ በጤና፣ በፋይናንስና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ በርካታ ስራዎችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ ስምምነቱና ድጋፉ ዘመናዊ ከተማ ለመፍጠር የሚደረገውን ስራ የሚደግፍ ነው ብለዋል።
የቱሪስት መዳረሻ ለሆነችው ሀዋሳ ለቱሪስቶችና ለከተማው ነዋሪዎች የተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ላደረገው ድጋፍ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።