ቀጥታ፡

የለሚ እንጀራ ማዕከል 2 ሺህ እናቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ያስችላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ "የለሚ እንጀራ ማዕከል" 2 ሺህ እናቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ በዓመት ውስጥ እስከ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት እንደሚያስችል የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ማዕከሉም እንጀራን በኢንዱስትሪ ደረጃ በመጋገገር በቀን 288 ሺህ እንጀራ መጋገር እንደሚያስችል ተገልጿል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የመጡ ከንቲባዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ለሚ እንጀራ ማዕከል በአጋር አካላት ተገንብቶ ለምርቃት የበቃ የትብብር ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ማዕከሉም እንጀራን በተሻለ ሁኔታ በኢንዱስትሪ በማምረት የእናቶችን ድካም የሚያቃልል እንደሆነ ተናግረዋል።

በማዕከሉም 2 ሺህ እናቶችን ጨምሮ በሌሎች ሥራዎችም አጠቃላይ እስከ 4 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር እንጀራን መረከብ የሚያስችል የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ነው ያነሱት። 

ማዕከሉም በቀን እስከ 288 ሺህ እንጀራ በመጋገር በሁለት ፈረቃ ከተሰራ በዓመት ውስጥ እስከ 3 ቢሊዮን ብር በአንድ ፈረቃ ከሆነ ደግሞ እስከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ብለዋል።


 

የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ከተማ ከንቲባዎች በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ከሚገኙ የልማት ሥራዎች ትምህርት እንዲወስዱ አደራ ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ በርካታ ውጤታማ የልማት ሥራዎች እንደተከናወኑ ጠቁመው፤ ድህነትን ማሸነፍ የሚያስችሉ የከተማ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

እንጀራን በማምረት ከአገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ወደ ውጭ ለመላክ የተደረገው የማዕከል ግንባታ በቀላሉ የማይታይ ስኬታማ ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል። 

ማዕከሉም የሴቶች፣ የእናቶችና እህቶችን የሥራ ዕድል ባለቤት በማድረግ ሕይወታቸው እንዲቀየር የተደረገው ጥረትም የሚያኮራና የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።


 

የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ፤ እናት ተኮር የሆነውን የለሚ እንጀራ ማዕከል አቅርቦትን በማሳደግ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ በመቀበል ፕሮጀክቱ በ341 ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታው መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥም ኦቪድ ግሩፕ 170  ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።  

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተወካይ አምባሳደር አሊ ሱሌማን፤ ሚድሮክ አዲስ አበባ ከተማ በሚካሄዱ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑን ተናግረዋል።

የእናቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያደርገው ፕሮጀክት ተሳትፎ ላደረጉት ኦቪድ ግሩፕ፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ መድህን ድርጅት፣ መታሰቢያ ታደሰ ኮንስትራክሽን፣ የታፑ ምግቦችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ተችሯቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም