ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለአገር አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23/2015 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለአገር አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፍተዋል፡፡

በምርቃቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሪዞርቱ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታም የአካባቢው ማህበረሰብ ነባር የኪነ-ሕንጻ ጥበብን ከዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውስጡም ፕሬዝዳንታዊ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ዘመናዊ መኝታ ክፍሎችና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን የያዘ ነው፡፡


 

ሪዞርቱ በተገነባበት ስፍራ የሚገኘው የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ሐይቅም በውሃ ላይ መዝናናት ለሚፈልጉ ጎብኝዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡

በተጨማሪም ቀደምት የዳውሮ ንጉስ ሃላላ የተገነባው የሃላላ ድንጋይ ካብ (ሃላላ ኬላ) ታሪካዊነቱን እንደጠበቀ በስፍራው ተጨማሪ የመስህብ አካል በመሆን ያገለግላል፡፡

የሪዞርቱ መገንባትም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም