በኦሮሚያ ክልል ልዩ የፈጠራ ችሎታና የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት እየተሰራ ነው--የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ልዩ የፈጠራ ችሎታና የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት እየተሰራ ነው--የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ
አዳማ ሚያዝያ 23/2015 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ልዩ የፈጠራ ችሎታና የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ገበያ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች፣ከተሞችና ዞኖች በስራ ፈጠራ አወዳድሮ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ፣የሜዳሊያና የሰርቲፊኬት እውቅና ሰጥቷል።
በዚህም በተወዳደሩበት የፈጠራና የቢዝነስ ሀሳብ ከ1 እስከ 3 ለወጡት ተወዳዳሪዎች ከ10 ሺህ እስከ 8 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ ልዩ የፈጠራ ችሎታና የቢዝነስ ሀሳብ ይዘው ከቀረቡት ውስጥ የተሻሉና አዋጭ የሆኑ 50 የፈጠራ ስራዎች ተለይተው እውቅና እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ካሣ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤
በክልሉ ስራ አጥነትን ለመቀነስ ኢንተርፕራይዞች ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው።
ለዚህም ልዩ የፈጠራ ችሎታና የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ድርሻቸው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በክልል ደረጃ የፈጠራ ችሎታውና የገበያ ሀሳባቸው ተለይቶ የአሸናፊዎች አሸናፊ ለሚሆኑት ተወዳዳሪዎች የተሻለ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ጠቁመዋል።
የፈጠራ ችሎታውን ይዘው በውድድሩ ከተሳተፉት መካከል ወጣት አድናን ሁሴን ከባዮ ጋዝ የመብራት ኃይል በማመንጨት የሚማርበት ትምህርት ቤትና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግሯል።
በውድድሩ አሸናፊ ከሆነ በሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍ አቅሙንና እውቀቱን ለማሳደግ እንደሚሰራበት ገልጾ ቀጣይ እገዛ እንዲደረግለት ጠይቋል።
ሌላኛው የውድድሩ ተሳትፊ ወጣት ሴና ተሰማ በውድድሩ የኦሮሞ የባህል አልባሳት የፈጠራ ውጤቶች ይዛ ማቅረቧን ተናግራለች።
በተለይ ይዛ የቀረበችውን የቢዝነስ ሀሳብ ወደ ገበያ በማስገባት በጨርቃ ጨርቅና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።