ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ):- ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ወላይታ ድቻ ከለገጣፎ ለገዳዲ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ27 ነጥብ 9ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ለገጣፎ ለገዳዲ በ11 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለቱን ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ለገጣፎ ለገዳዲ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ሁለት ጊዜ ተሸንፏል በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 4 ለ 3 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የ22ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በደረጃ ሰንጠረዡ ፋሲል ከነማ በ30 ነጥብ 8ኛ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና በ31 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ፋሲል ከነማ ካለፉት የአምስት ሊግ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል።
በአንጻሩ ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
በተያያዘ ዜና ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከተደረጉ በኋላ የውድድሩ የአዳማ ቆይታ እንደሚጠናቀቅ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
ቅዳሜ ሚያዚያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከሚካሄዱ ሁለት የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ 27ኛ ሳምንት ያለው መርሐግብር በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚደረጉም ገልጿል።