ቀጥታ፡

ከ200 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች በአዲስ አበባ የለውጡ ስኬት ማሳያ የሆኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ)፦ ከ200 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች በአዲስ አበባ የለውጡን ስኬት ማሳያ የሆኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።


 

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትሰሰር ገጻቸው “ከ200 በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች በአዲስ አበባ ከለውጡ ወዲህ አቅደን በመፈፀም ያስገኘናቸዉን ስኬቶችንና ዉጤታችንን ያሳዩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም ሰው ተኮር ስራዎቻችንን አስጎብኝተናቸዋል” ብለዋል።


 

“በመቀጠልም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የበለፀጉ ከተሞችን ለመፍጠር ከንቲባዎች በሚጫወቱት ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገን ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ተቀብለናል” ሲሉም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ የከተማዋ ገጽታ ተቀይሮ የቱሪስት መዳረሽ ሆናለች ያሉት ከንቲባዋ ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን በጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችል የስራና የአሰራር ባህል ተፈጥሯል በማለት ገልጸዋል።


 

በመዲናይቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አለሁ የሚል አሳቢ አመራር መፈጠሩንም አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች ከዚህ ስኬት ልምድ ወስደው ከተሞቻቸውን የማላቅ እና የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉ ሰው ተኮር ስራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም