በቀን 288 ሺህ እንጀራ የሚጋገርበት ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በቀን 288 ሺህ እንጀራ የሚጋገርበትና እንጀራን ኢንዱስትራላይዝ በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ለሚ እንጀራ ማዕከል ተመርቋል፡፡

ማዕከሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች ጋር በመሆን መርቀዋል፡፡


 

ለሚ እንጀራ ማዕከል የእናቶችን ድካም የሚያቀልና እንጀራን ከፍ ባለ ደረጃ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው gገልጸዋል፡፡

"ማዕከሉ ከፈተናዎቻችን በላይ ሆነን የማይቻል የሚመስለውን የመቻላችን ማሳያ ነው" ብለዋል ፡፡

በየቦታው ያለንን አቅም፣ ገንዘብ እና እውቀት በማስተባበር የነዋሪዎችን ሸክም የሚያቀሉ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እየተገበርን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የእንጀራ ማዕከሉ ከ2 ሺህ እናቶች በተጨማሪ በተለያዩ የስራ መስኮች ለ1ሺህ ነዋሪዎች በጠቅላላው ለ3 ሺህ ወገኖች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ነጥቀሳቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡


 

በዚህ የእናቶችን ሸክም በዘላቂነት በሚያቀለው ታላቅ ስራ ላይ ያገዙን ልበ ቀና ባለሃብቶችን ማለትም ኦቪድ ግሩፕ 170 ሚሊየን ብር፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 75 ሚሊየን ብር፣ መድህን ድርጅት 20 ሚሊየን ብር፣ መታሰቢያ ታደሰ ኮንስትራክሽን 500 ዘመናዊ ምጣዶችን በማቅረብ እንዲሁም የታፑ ምግቦች ደግሞ በማማከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከንቲባ አዳነች በእናቶቹ ስም አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም