የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ጽንፈኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል-አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ጽንፈኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል-አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2015(ኢዜአ)፡-የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ጽንፈኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን ሽኝት መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ዘመድ አዝማዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ቤተሰቦች የአበባ ጉንጉን አኖረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት አቶ ግርማ የሺጥላ ሀገራዊ ራዕይ የሰነቁ በሳልና ቆራጥ የህዝብ አገልጋይ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
ለፍትህና ለእውነት የቆሙ የብልጽግና አመራር እንደነበሩ አስታውሰው ለሀገርና ለህዝብ ብሎም ለፓርቲው የነበራቸው አበርክቶ መቼም አይረሳም ብለዋል።
አቶ ግርማ ለአገርና ለህዘብ ጥቅም ሌት ተቀን እየሰሩ እያሉ በጽንፈኞች እኩይ ዓላማ የህይወት መስዋእትነት መክፈላቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በጽንፈኞች እኩይ ድርጊት ፈፅሞ ሊደናቀፍ አይችልም ብለዋል።
የፅንፈኞች እኩይ ዓላማ ሊሳካ የማይችል መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብን መሪና ንጹሃንን በመግደል ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ አካላት ዋጋ የሚያስከፍላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት በጥብቅ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠው የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በግርማ የሺጥላ ላይ በጽንፈኞች የተፈፀመው ግድያ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የተቃጣ የመከራ በትር መሆኑን ገልጸዋል።
በግርማ የሺጥላ ላይ በጽንፈኞች የተፈፀመው ግድያ ክልሉን የጦር አውድማ ለማድረግና የህዝቡ ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የታለመ የጥፋት እቅድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመጠፋፋት ላይ ተመስርቶ ህዝብን በማዳከምና የጥቃት ተጋላጭ በማድረግ የከፋ ችግር ላይ ለመጣል መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የጽንፈኞችን እኩይ ዓላማ በጋራ ትግላችን በማክሰም ዘላቂ ሰላምና ልማታችንን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።
የጽንፈኞቹ ተግባር ለዘመናት የተገነባውን ልማት የሚያወድም፣ የተጀመረውን የሚያሰናክልና ቀጣይ እቅዶችን የሚያከሽፍ በመሆኑ በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በፅንፈኞቹ የተፈፀመው ጥቃት በጽናት በጋራ እንድንቆም የሚያደርገን አንጂ በፍፁም ወደ ኋላ የሚመልሰን አይሆንም ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የአቶ ግርማ ህልፈተ ህይወት "የኖረለትንና የተሰዋለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንድንጸና ያደርገናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የአቶ ግርማ ሞት የያዝነው ዓላማ ሊገደል የሚችል አለመሆኑን ለማሳየት የበለጠ የታጠቅንበት ነው ብለዋል፡፡
የለውጡ ጉዞ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስና በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ አቶ ግርማ ራሱን ሰጥቶ የታገለ ጀግና ነበር ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአቶ ግርማ ዓላማ የህዝቦች አንድነት፣ ወንድማማችነት እንዲሁም የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም ማንም ሰው ሥጋን እንጂ ዓላማን መግደል አይችልም ያሉት ከንቲባዋ ግርማ የተሰዋለት ዓላማ በሁላችንም የጋራ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የፅንፈኞች የጥፋት ዓላማ ጠፊ እንጂ በፍፁም ቀጣይነት አይኖረውም ብለዋል ከንቲባዋ።