ቀጥታ፡

የኒጀር፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ኮትዲቯር የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2015(ኢዜአ)፦ የኒጀር፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ኮትዲቯር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።


 

የልኡካን ቡድኑ አባላት ከኒጀር፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ኮትዲቯር የተውጣጡ የግብርና፣ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝና ሌሎች ተቋማትን የወከሉ ሚኒስትሮችንና ሌሎች የስራ ኅላፊዎችን ያካተተ ነው።


 

በኢትዮጵያ ለአራት ቀናት በሚያደረጉት የስራ ጉብኝትም የተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ ተብሏል።

በሚኖራቸው ቆይታ በኦሮሚያ ክልል የስንዴ፣ የአቮካዶና የቡና ልማት ስራዎችን የሚጎበኙ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አማካሪ ዶክተር ያሬድ ተሾመ ገልጸዋል።


 

በአፍሪካ በድህነት ቅነሳ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉብኝቱ የጎላ ጠቀሜታ ያለው መሆኑም ተመላክቷል።

በአፍሪካ መሰል የልምድ ልወውጦችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም