ጽንፈኝነት የሚያመጣውን መሪር ሃዘን ተረድተን በመታገል ከስር መሰረቱ መንቀል አለብን--አቶ ፍቃዱ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
ጽንፈኝነት የሚያመጣውን መሪር ሃዘን ተረድተን በመታገል ከስር መሰረቱ መንቀል አለብን--አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2015(ኢዜአ)፦ ጽንፈኝነት የሚያመጣውን መሪር መከራና ሃዘን ተረድተን አምርረን በመታገል ከኢትዮጵያ ምድር ከስር መሰረቱ እንዲነቀል ማድረግ አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ።
የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን ሽኝት በወዳጅነት አደባባይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች በተገኙበት ተካሒዷል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ፍቃዱ ተሰማ “ግርማ ለቆመለት ዓላማ የኖረ በመጨረሻም አይተኬ ህይወቱን ለህዝብና ለሃገሩ የሰጠ ውድ የህዝብ ልጅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ግርማ ሃገር ህዝብና መንግስት የሰጠውን ታሪካዊ ሃላፊነት በፍጹም ቆራጥነት ተወጥቷል ያሉት አቶ ፍቃዱ እሱ ቢሞትም ሃሳቡ ዓላማው የሚሊዮን ጓደኞቹና የኢትዮጵያ ሃሳብ በመሆን ሳይንጠባጠብ ይሻገራል ብለዋል።
የስራ ባልደረቦቹ የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ህዝቡም ጽንፈኝነት የሚያመጣውን መከራና መሪር ሃዘን ተረድተን አምርረን በመታገል ስር መሰረቱ ከኢትዮጵያ እንዲነቀል ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።