ግርማ የቆመለት የህዝቦች ወንድማማችነት፣ አብሮነትና የኢትዮጵያ ብልጽግና ይቀጥላል--ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ግርማ የቆመለት የህዝቦች ወንድማማችነት፣ አብሮነትና የኢትዮጵያ ብልጽግና ይቀጥላል--ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2015(ኢዜአ)፦ ግርማ የቆመለት የህዝቦች ወንድማማችነት፣ አብሮነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና ይቀጥላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን ሽኝት በወዳጅነት አደባባይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የሟቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች በተገኙበት ተካሒዷል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት አቶ ግርማ ቢሞቱም እሳቸው የቆሙለት እውነት ግን የሚቀጥል ነው።
“ግርማን ገድለውታል፣ ግርማ የቆመለት እውነት ግን ይቀጥላል” ያሉት ከንቲባዋ “እሱም የህዝቦች ወንድማማችነት፣ የህዝቦች አብሮነት፣ የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሰላም ፣የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው” ብለዋል።
የግርማን ሞት መሥማት አብረነው ለሰራነው ለእኛ አሳዛኝም፤ አስደንጋጭም ነበር ያሉት ከንቲባዋ ግርማ የማይሞት ዓላማ ያነገበ መሪ ነው ብለዋል፡፡
“ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቅ መሪ ነበር” ያሉት ከንቲባዋ ግርማ የሕዝቦች ወንድማማችነት እና የኢትዮጵያ አንድነት የሚያስጨንቀው መሪ ነበርም ሲሉ ተናግረዋል።