የህዝብን መሪ እየገደሉና የዜጎችን መብት እየገፈፉ የሚረጋገጥ ዘላቂ ጥቅም የለም - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን መሪ እየገደሉና የዜጎችን መብት እየገፈፉ የሚረጋገጥ ዘላቂ ጥቅም የለም - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2015(ኢዜአ)፦የህዝብን መሪ እየገደሉና የዜጎችን መብት እየገፈፉ የሚረጋገጥ ዘላቂ ጥቅም አለመኖሩን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የአቶ ግርማ የሺጥላ አስከሬን ሽኝት መርሃ ግብር የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሔደ ይገኛል።
በዚሁ ጊዜ መልእክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በአቶ በግርማ የሺጥላ ላይ በተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ የተሰማቸውን መሪር ሀዘን ገልጸዋል።
አቶ ግርማ የሺጥላ ልዩነት ሰባኪነትን የሚጸየፉና ጽንፈኝነትን አምርረው የሚታገሉ አመራር እንደነበሩም ተናግረዋል።
ከምንም ነገር በላይ የህዝብንና የአገርን ዘላቂ ጥቅም የሚያስቀድሙ በጋራ መበልጸግን የሚመኙ እንደነበሩም ገልፀዋል።
ለሀገርና ህዝብ ያበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ መቼም የሚረሳ አለመሆኑን ጠቅሰው ዓላማቸውን ለማሳካት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
አቶ ግርማን የገደሉት ወደ አውሬነት የተቀየሩ ጽንፈኞች ናቸው፤ ያሉት አቶ አደም የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በአጥፊዎች እንደማይደናቀፍ ተናግረዋል።
መሪዎችን በመግደልና የዜጎችን መብት በመግፈፍ የሚረጋገጥ ዘላቂ ጥቅም አለመኖሩን ገልጸዋል።
መሪን መግደልና ህዝብን ማሰቃየት ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልጸው የአቶ ግርማን ገዳዮችና ጽንፈኞችን ለህግ ለማቅረብ አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመቆም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረቡን ስራ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
ለአቶ ግርማ ቤተሰቦች፣ ለአማራ ክልል ህዝብ፣ ለብልጽግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።
ከአቶ ግርማ የሺጥላ ጋር ለተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦችም በተመሳሳይ ፈጣሪ መጽናናት እንዲሰጣቸው ተመኝተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ከአቶ ግርማ የሺጥላ ቤተሰቦች ጎን እንደሚቆምም አረጋግጠዋል።