መላው ሕዝብ ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን ዕኩይ ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ፅንፈኞችን ማጋለጥ አለበት -የደቡብ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
መላው ሕዝብ ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን ዕኩይ ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ፅንፈኞችን ማጋለጥ አለበት -የደቡብ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሀዋሳ ሚያዝያ 21/2015(ኢዜአ)፦ መላው ህዝብ ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን ዕኩይ ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ፅንፈኞችን ማውገዝና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማጋለጥ እንዳለበት የደቡብ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመለከተ።
የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ጸዳለች ሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ፅንፈኞች ፍላጎታቸውን በኃይል በመጫን የሀገርን የለውጥ ጅማሮ ለማደናቀፍ እኩይ ተግባር እየፈጸሙ ነው።
እነዚህ የ"እኔ ብቻ" የሚሉ ፅንፍ የያዙ አካላት የመንግሥትና የሕዝብ አደራ ይዘው የሚደክሙ አመራሮችን በመግደል በሕዝብ ውስጥ ስጋት ለመፍጠር እየሞከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ድርጊታቸውን ሊያወግዝና እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ፅንፈኞች ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ ስጋት በመፍጠር ሀገርን ለማተራመስ እየፈጸሙት ያለውን እኩይ ተግባር እንደሚያወግዙ ገልጸው፤ መንግሥትም የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።
በግድያ የሚለወጥ ነገር እንደሌለ ጠቅሰው በዚህ ተግባር ላይ የተሰማራ ማንኛውም አካል ከፅንፈኝነት አመለካከት ራሱን ማጽዳት አለበት ብለዋል።
ህዝብም ጽንፈኞችን አጋልጦ ለህግ መስጠት እንዳለበት ነው የተናገሩት።
"ህዝብና ሀገር ሲኖር ነው ሀሳባችንን መሸጥና የምንፈልገውን ማሳካት የምንችለው" ያሉት ወይዘሮ ጸዳለች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚያራምዷቸውን አመለካከቶች በሰላማዊ መንገድ በህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ መስራት አለባቸው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮነትን የሚሸረሽር ፅንፍ ከያዘ አቋምና አተያይ በመላቀቅ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ ምክር ቤቱ በዚህ ልክ ተግባሩን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ፅንፈኝነት በፖለቲካው አደጋ ውስጥ እንድንገባ በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን የማደናቀፍ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
“በግልም ሆነ እንደ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህን ድርጊት በፅኑ አወግዛለሁ'' ያሉት ወይዘሮ ጸዳለች ''መላው ሕዝብ ፅንፈኝነትን ለማስቆም በሚደረገው ትግል ውስጥ ከመንግሥት ጎን በመቆም እኩይ ተግባር የሚፈጽሙትን መታገልና ማውገዝ አለበት” ብለዋል።
እንዲሁም ጠንካራ አንድነትና መግባባትን የሚሸረሽር ማንኛውንም ፅንፍ የያዘ አካል መታገል እንደሚገባው ምክትል ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።