ቀጥታ፡

መንግሥትና ሕዝብ ለጋራ ዘላቂ ሰላም በፅንፈኞች ላይ እርምጃ መውስድ አለባቸው--የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2015(ኢዜአ)፦መንግሥትና ሕዝብ ለጋራ ዘላቂ ሰላም በፅንፈኞች ላይ እርምጃ መውስድ አለባቸው ሲል የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢብሳ ነጋዎ ለኢዜአ እንደገለጹት በአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ላይ የተፈጸመው ግድያ የሚወገዝ ነው።

ፅንፈኝነት የሕዝብን የበላይነትና ታሪክ ሰሪነት ያለመቀበልና ሁሉም ነገር 'እኔ ያልኩት ይሁን' ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ፅንፈኝነት የግለሰብ ጀብደኝነትን ተከትሎ በሽፍትነትና በጉልበት ነገሮችን ለማስፈጸም መሞከር መሆኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካ አካሄዳቸውም መድብለና ፓርቲና ሁሉን አካታች የሆነውን መንገድ ከመቀበል ይልቅ ሃሳባቸውን በጠብ መንጃና በሽብር ለመጫን መፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ሂደት ደግሞ ሕዝቦችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ መፈለጊያ መንገድ እንጂ በህዝብ ድምፅ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ አለመሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህ ዘመን በሰለጠነ መንገድ በምክክርና በውይይት የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እየተቻለ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ መታየቱ አሳሳቢ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዘመናት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ግድያን ሽፋን በማድረግ ስልጣንን ለመቆጣጠር እስከ ዛሬ መፈጸሙ ካለፈው ያለመማርም ችግር በመሆኑ ይህ ሁኔታ መገታት አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የፖለቲካ ስራዎችን ለማከናወን መወሰን አለባቸው ብለዋል።

እንደ አቶ ኢብሳ ገለጻ መንግሥት የተመሰረተበት ዋና ዓላማ የሕዝቦችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ በመሆኑ ይህን ግዴታውን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በዚህ ሂደት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሰላምን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ፅንፈኝነትን በመቃወም የመንግሥትን እርምጃ መደገፍ አለበት ብለዋል።

የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአማራ ክልል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ትናንት ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም