ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን --የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ አመራሮችና አባላት

ድሬደዋ ሚያዚያ 21/2015 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሴቶች ሊግ አመራሮችና አባላት ተናገሩ።

"እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ሃሳብ የድሬዳዋ የብልጽግና ፓርቲ የድሬደዋ ቅርንጫፍ የሴቶች ሊግ ፅህፈት ቤት አመራሮች እና አባላት ለአንድ ወር የሚዘልቅ የህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ንቅናቄ ዛሬ በድሬዳዋ ጀምረዋል ።

የሊጉ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሁክሚያ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለአንድ ወር በገጠር እና በከተማ የሚካሄደው የሴቶች ንቅናቄ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ይከናወናል።

ዛሬ በተካሄደው የንቅናቄው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር የቦንድ ግዢ የሊጉ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከ200 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዢ መፈፀማቸውን ገልጸዋል።

የቦንድ ግዢ የፈፀሙት የሊጉ አባል ወይዘሮ ሄላሊ አብዱራህማን በበኩላቸው ለአገር እና ለትውልድ ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጣው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

"ግድቡ ልጆቼ እና የነሱ ዘመን ትውልድ የፈነጠቀ የህልውናችን መሠረት ሆኗል" ብለዋል።

የሊጉ አባል ወይዘሮ አለም አይናለም በበኩላቸው ለግድቡ የተዘጋጀውን ቦንድ ለአራት ግዜ ከመግዛት ባሻገር ዘንድሮ የቀበሌያቸው ሴቶችን በማስተባበር ከ86 ሺህ ብር በላይ ቦንድ ግዢ እንዲከናወን ማድረጋቸውን አስረድተዋል።


 

"የታሪካችን አዲስ አሻራ የሆነው ዘመን ተሻጋሪ ግድብ ዳር እስኪደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

በንቅናቄው ማስጀመር ላይ የተሳተፉት የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት ንቅናቄው በድሬደዋ የሚካሄደው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ ወርሃዊ የሴቶች ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የከተማው ሴቶች ተሳትፏቸው የሚያጠናክሩበት ነው ብለዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዢ እና በስጦታ መበርከቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም