ግምታዊ ዋጋቸው ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ግምታዊ ዋጋቸው ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከሚያዚያ 13 እስከ 19 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 214 ነጥብ 4 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 43 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 258 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አመልክቷል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣መድሃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይትና የተለያዩ አገር ገንዘቦች ይገኙበታል ፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬድዋ፣ሞያሌና እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መሆናቸውንና በቅደም ተከተላቸው 116 ሚሊዮን 27 ሚሊዮን እና 25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ እቃዎችን መያዛቸው ተጠቁሟል።
የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣በፌደራል ፖሊስ፣በክልል ፖሊስ አባላትና ሕብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 10 ግለሰቦች እና ሶስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመልክቷል።
የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ሕብረተሰቡ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።