ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደተሳተፉበት የተገለጸው “ከፍታ የወጣቶች ፌስቲቫል” ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደተሳተፉበት የተገለጸው “ከፍታ የወጣቶች ፌስቲቫል” ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21/2015 (ኢዜአ):- ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደተሳተፉበት የተገለጸው “ከፍታ የወጣቶች ፌስቲቫል” ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ተጀምሯል።
ፌስቲቫሉ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ(ዩኤስአይዲ)፣ማሪፍ ኢትዮጵያና ሌሎች አጋር አካላት ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ “ወጣትነት ለአገር ግንባታ፣ለነገ ስኬት፣ለለውጥና ስራ ፈጠራ መልካም ስብዕናን በመላበስ በንቃት የሚጥሩበት የሽግግር ዕድሜ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥር በመጠቀም ለማልማት መንግስት ለወጣቶች ጉዳይ ትኩረት በማድረግ ምቹ ፖሊሲዎችን የአሰራር መዋቅሮችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“ወጣቶች ለሰላም ትኩረት በመስጠት በምክንያታዊነት በማመን ራሳቸውን ከጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያነት ሊከላከሉ ይገባል” ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
የወጣቶች ፌስቲቫሉ ወጣቶችን ለመልካም ጉዳዮች ለማነቃቃት፣ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማሳደግና አዳዲስ መንገዶችን ለማመላከት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከመላው የኢትዮጵያ ከተሞች የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል።
ወጣቶች ከስኬታማ የንግድና የትምህርት ዓለም ግለሰቦች ጋር ለማስተሳሰር የልምድ ልውውጥ ስልጠናዎች እንደሚኖሩም ተገልጿል።