ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማስመልከት በተካሄደው የሩጫ ውድድር በወንዶች አቤል በቀለ በሴቶች ኮከቤ አበራ አሸነፉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አስመልክቶ ዛሬ በተካሄደው የአምስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር በወንዶች አቤል በቀለ በሴቶች ኮከቤ አበራ አሸንፈዋል።

በውድድሩ ላይ ከሶስት ሺህ በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

“ለኢንዱስትሪ እንሩጥ” በሚል በተካሄደው ውድድር ባለሃብቶች አትሌቶችና ሌሎችም ግለሰቦች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በውድድሩ በወንዶች አቤል በቀለ ሲያሸንፍ ነጋሳ ቀቃባ እና አለፎም ተስፋዬ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። 


 

በሴቶች ኮከቤ አበራ አሸናፊ ሆናለች። ፋንቱ ሹጌ እና ጫልቱ ዲድአ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።
ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል የ100፣የ50 እና 25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴአታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል ኢንዱስትሪውን ለማበረታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ደግሞ የአምራች ኢንደስትሪውን ለማስተዋወቅ በኢንዱስተሪ ሚኒስቴር አማካኝነት የ 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮች መከናወናቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪው በመሳብና ሕብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህሉ እንዲጨምር የማስተዋወቂያ መድረክ እንደሚሆን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ለቀጣይ 10 ዓመት እንደሚቀጥልና በስፖርትና በተለያዩ መንገዶች ንቅናቄ በመፍጠር ተቋማዊ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2 2015 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም