የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሐብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሐብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ደረሰ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 21 / 2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሐብት 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተገለጸ።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ123 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሁሉም መመዘኛዎች መልካም አፈፃፀም እንደነበረው አስታውቀዋል።
በቀጣይ በተለይ ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች በሆኑት በተቀማጭ ሃብት አሰባሰብ፣ በዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ በብድር አሰጣጥና አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲሁም የባንኩን የሪፎርም ስራዎች በማስቀጠል በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ባንኩ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ ብድር በመስጠትና በመሰብሰብ፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና አቅርቦት እንዲሁም በሌሎች ፋይናንስና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ አፈፃፀሞች ውጤታማ ስራ መሰራቱ ተጠቁሟል።
የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ባንኩ ወጤታማ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዲጂታል ባንክ አማራጮች ብቻ 2 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር መንቀሳቀሱን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ የስራ አመራሮች፣ የዲስትሪክቶች ዳይሬክተሮች እና የልዩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል፡፡