ቀጥታ፡

መንግሥት ፅንፈኞች ላይ የማያዳግም አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለበት- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ሚዛን አማን ሚያዝያ 21 / 2015 (ኢዜአ) ፦ ሕግና ሥርዓትን ማስጠበቅ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ እኩይ ተግባር በሚፈጽሙ ፅንፈኞች ላይ መንግሥት የማያዳግም አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ አለበት ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመለከተ።

የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት በላከው መግለጫ ፅንፈኛ ኃይሎች በአማራ ክልል ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር ሲጥሩ መቆየታቸውን ጠቅሶ፤ የጋራ ግብረ ኃይሉ ይህን ተከትሎ አስፈላጊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን መግለፁ ይታወቃል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ፣ ለኢዜአ እንደገለጹት ሕግና ሥርዓትን ማስጠበቅና ማስከበር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው።

እንደ ሀገር የፖለቲካ ምህዳር እንዳልሰፋና የሃሳብ ነፃነት እንደሌለ በማስመሰል ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን እኩይ ተግባር በሚፈጽሙ ፅንፈኞች ላይ መንግሥት የማያዳግም አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።

በሃሳብ የበላይነትን መያዝ እየተቻለ ሃይልን በመጠቀም የራስን ፍላጎት ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ዘመኑን የማይመጥን በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለውም ገልጸዋል።

"እኛም የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት እንሰራለን" ሲሉ አረጋግጠው፤ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ሕግ የማስከበር ተግባሩን መደገፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ግለሰብን ጨምሮ የትኛውም አካል ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ አለበት ያሉት አቶ ግርማ፤ የፅንፈኝነት ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ለጊዜው የዜጎችን ደህንነት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማወክ በስተቀር አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ አይችሉም ብለዋል።

"እንደ ፓርቲ በተለያየ የፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ ብንገኝም የምንሰራው ለሕዝብና ለአንድ ሀገር ነውና የልዩነት አጀንዳዎችን በማጥበብ የተፈጠረውን የፖለቲካ ምህዳር አስፍቶ በማየት ለጋራ አጀንዳ መስራት አለብን" ብለዋል።

የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ለማንኛውም ጤነኛ ሰውና አደረጃጀት ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ "ተሰባስበን በአንድነት ሀገርን በሰላማዊ መርህ ማገልገል ከሁላችንም ይጠበቃል" ብለዋል።

ሃሳብን በሃሳብ የበላይነትን እንዲያገኝ አድርጎ መሄድ እየተቻለ በኃይል የበላይ ለመሆን የሚደረግ ሙከራ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ሲሉ አቶ ግርማ በአፅንኦት ገልጸዋል።

አክለውም ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰ ፅንፈኝነትን ማራመድ በፍጹም ያለንበትን ዘመን የማይመጥን ተግባር ነው ሲሉም ኮንነዋል።

ፅንፈኝነት በእንጭጩ ካልተቀጨ ለመጪው ትውልድ ጭምር መጥፎ መንገድ የሚከፍት መሆኑንም አመላክተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት በአቶ ግርም የሺጥላ ላይ ሰሞኑን በፅንፈኞች የተፈጸመውን እኩይ ተግባር በጋራ ምክር ቤቱ በፅኑ የሚወገዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ጋር የጥፋት ተግባሩን ማወገዝ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በምንም አይነት መንገድ ወደ ፅንፈኝነት አስተሳሰብ እንዳይሳቡና የእኩይ ተግባር ተሳታፊ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ ግንዛቤ ፈጥረው እንዲመሩም መክረዋል።

የአመለካከት ልዩነት ቢኖረን እንኳ በመነጋገር ችግሮችን መፍታት እንጂ የኃይል እርምጃ አማራጭ ለሀገር የሚጠቅም አይደለም ያሉት ደግሞ በክልሉ የቤንች ሸኮ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ክፍሌ ሽፈራው ናቸው።

ፅንፍ ይዞ እኩይ ተግባር መፈጸም አደገኛ ነው ያሉት፤ ሰብሳቢው በብልፅግና ፓርቲ በአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ ሰሞኑን የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ፓርቲ እናወግዛለን ብለዋል።

ድርጊቱ የአስተሳሰብ መስመርን የለቀቀ ሲሆን፤ በውይይት የማመን ብቃትና የዴሞክራሲ ባህል የጎደላቸው ፅንፈኞች የፈጸሙት እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝብን ሰላምና መረጋጋት አስቀድሞ መንቀሳቀስ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡ ፅንፈኝነት አጥብቆ በመቃወም የሰላም አማራጭን ለይቶ መደገፍ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም