ቀጥታ፡

የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል---ምሁራን

ጅማ  ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ) ፡- የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል ለዘላቂ ሰላም የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ችግሮችን በሰላማዊና በውይይት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን እንዳሉት መንግስት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የነበረውን ግጭት በሰላም ፈትቶ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ችግሮችም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ አቶ አክሊሉ ኪዳኔ፤ ችግሮችን በሰላማዊና በውይይት መፍታት ሁልጊዜም ለአገርና ለዜጎች ዘላቂ ሰላም ጠቃሚ ነው።

ችግሮችን በሀይል ለመፍታት መሞከር አገርን ለውድመት እንዲሁም ዜጎችን ለሞት፣ ለእንግልትና ለስደት ከመዳረግ ውጪ ፋይዳ የለውም ብለዋል።

የሀይል እንቅስቃሴዎች የተለያዩ አገራትን ወደማይወጡበት ችግር የከተተ  መሆኑንም አቶ አክሊሉ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"በኢትዮጵያም ቢሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ከፍተኛ ቁሳዊና ሰብዓዊ ቀውስ ማድረሱን ማስታወስ ይቻላል" ብለዋል።

በመሆኑም የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አቶ አክሊሉ አስገንዝበዋል።

አሁን እንደመንግስት የተጀመሩ የሰላም ስራዎች በሰላም እጦት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችና ተቋማት ለማቋቋም ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑንም አክለዋል።

ሕዝቡ የሰላምን ዋጋ ተረድቶ በመንግስት በኩል የተጀመሩ ስላምን የማጽናት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው "የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና የውስጥ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ልምድ ልናዳብር ይገባል" ይላሉ።

"የውስጥ ችግሮቻችን ተደማምጠን እና ተወያይተን መፍታት ባለመቻላችን ለዘመናት በብዙ ችግሮች ውስጥ ቆይተናል'' ነው ያሉት።

በመሆኑም መንግስት የጀመራቸው የሰላም ሂደቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ያነሱት ምሁሩ አሁንም የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የተሟላ ሰላም እንዲኖር ማስቻል ያስፈልጋል።

መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ሕዝቡ በንቃት መሳተፍና ማገዝ እንዳለበትም መክረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም