በድሬዳዋ የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ
ድሬዳዋ ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ) ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት የሚተገበረው የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር በድሬዳዋ ደረጃ በይፋ ተጀመረ።
በመርሃ ግብሩ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር ስራ አስኪያጅ አቶ ከበሩ በላይነህ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ መርሃ ግብሩ ለሚቀጥሉት ሰባት አመታት ውሃ ገብ በሆኑ የአገሪቱ ገጠራማ ክፍሎች በሙሉ ይተገበራል።
መርሃ ግብሩ በግብርናው ዘርፍ የተቀመጠውን የ10 አመት መሪ ዕቅድ ውጤታማ በማድረግ እየተመዘገበ የሚገኘውን ምርትና ምርታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ ከማሳ እስከ ገበያ ያሉትን የዘርፉን ሰንሰለቶች በጥናት ተመስርቶ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አቶ ከበሩ አስታውቀዋል።
በዚህም በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአፈር እና በውሃ ጥበቃ፣ በመስኖ ልማት የተጀመሩ አበረታች ስራዎች በውጤት ለማጀብ ያስችላል ብለዋል።
የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና የቤተሰብ አቅም በመገንባት መሠረታዊ ውጤት የሚያመጣውን መርሃ ግብር በየደረጃው የሚገኙ ፈፃሚና አስፈፃሚ ተቋማትና ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት ተቀናጅተው እንዲተገብሩ ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ የእንሰሳትና የሰብል ልማት ይጎለብታል፤ መሠረተ ልማቶች ይገነባሉ፤ 35 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በዘላቂነት ይለማል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ መርሃ ግብሩ የምግብ ዋስትና ጥያቄ በመመለስ በግብርናው ዘርፍ የተጀመረውን ስራ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
መርሃ ግብሩ ቀደም ሲል በግብርና ዘርፍ የተጀመሩትንና ውጤት የተገኘባቸውን ስራዎች እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።
በቢሮው የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ስሻው አያሌው በበኩላቸው መርሃ ግብሩ በ21 ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በመስኖ፣ በእንሰሳት፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች በማከናወን 18 ሺህ የሚጠጉ ቤተሰቦች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።
በመንግስትና በተለያዩ አለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ትብብር በ685 ሚሊዮን ብር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበረው "የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር" የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ መደረጉን ይታወሳል።