"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተጀመረበት አንደኛ ዓመት በማስመልከት በሚሊኒየም አዳራሽ የንግድ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተጀመረበት አንደኛ ዓመት በማስመልከት በሚሊኒየም አዳራሽ የንግድ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት በሚሊኒየም አዳራሽ የንግድ ኤክስፖ ሊካሄድ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድ ኤክስፖው ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 2/2015 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል ተብሏል።
በንግድ ኤክስፖው ከ350 በላይ ትላልቅ የኢንዱስትሪ አምራች ባለሃብትና ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ነው የተጠቆመው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሃሰን መሃመድ "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሚያዚያ 28/2014 ዓ.ም ተጀምሯል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተጀመረበት አንደኛ ዓመት በማስመልከት አዲስ አበባ በሚገኘው ሚሊኒየም አዳራሽ የንግድ ኤክስፖ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት የንግድ ኤክስፖ ላይም ከ350 በላይ ትላልቅ አምራች ባለሃብቶችና ኩባንያዎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።
የተለያዩ የአገር ውስጥ ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ እንደሚቀርቡም ነው የጠቆሙት።
የንግድ ኤክስፖው የአገር ውስጥ ምርትን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና የውጭ ንግድ ሥርዓት ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ምላሽ መስጠት ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ከኃይል አቅርቦት፣ ከውጭ ምንዛሬ፣ ከመሰረተ ልማትና ከግብዓት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ንቅናቄውም ተዘግተው ሥራ ያቆሙ 219 ፋብሪካዎችን ጭምር ወደ ሥራ እንዲመለሱ በማድረግ ወጣቶች በሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገበት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።
የገቢ ምርቶችን በመተካት ሂደትም የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለም ተናግረዋል።
የተማሪ ቦርሳ፣ ጫማ፣ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ በአገር ውስጥ ፋብሪካዎች እንዲመረት በማድረግ በሙከራ ደረጃ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ እንደተጀመረ ጠቁመዋል።
ጅምሩን በማጠናከር እንደ ባሕርዳር ያሉ ሌሎች ትላልቅ የኢትዮጵያ ከተሞች የተማሪ ደንብ ልብስ ለማቅረብ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን ምርቶች ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር የግብይት ትስስር በማድረግ በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን የገበያ ትስስር ችግር ምላሽ እንዲያገኝ እየተደገረ መሆኑንም አመላክተዋል።