በትግራይ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ከ6 ሺህ በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ከ6 ሺህ በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው
ጅግጅጋ ሚያዚያ 20/2015 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል አጋጥሞ በነበረው ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ 6ሺህ 378 አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለፉት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ሰሞኑን በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረ ሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኢንተርፕራይዞቹን ወደ አገልግሎት ለማስገባት በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ኢንተርፕራይዞቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የሰላም ስምምነቱ ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በሰላም ስምምነቱ መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የአምራች ኢንተርፕራይዞችን መልሶ ሥራ ለማስጀመር የሶስት ወር ዕቅድ አውጥቶ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞቹን አገልግሎት ለማስጀመር የተለያዩ የማነቃቂያ መድረኮችን ከማካሄድ ጀምሮ የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በበኩላቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የዘርፉ ተወካዮች በመድረኩ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ይህም የተደረሰው የሰላም ስምምነቱ አካልና የሰላም ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ትግራይ ክልል የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችን ወቅታዊ ሁኔታ በመለየትና በመደገፍ መልሶ ለአገልግሎት ለማብቃት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በክልል የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለክልሉ ብሎም ለሀገር ያላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኢንተርፕራይዞቹን መልሶ ወደ አገልግሎት ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጀመሩን ዶክተር አለባቸው አስታውቀዋል።