ለሦስት ቀናት የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም የውጭ ኩባንያዎች በመሳብ ውጤት አስገኝቷል - የኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ለሦስት ቀናት የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም የውጭ ኩባንያዎች በመሳብ ውጤት አስገኝቷል - የኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2015(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ እድል የፈጠረ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው "ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ፎረም" ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፎረሙ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅ የቻለችበት ነው።
ያም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ አስችሏል ብለዋል።
በዚህም አዳዲስ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲገቡ ፎረሙ እድል መፍጠሩን አብራርተዋል።
ይህንንም ተከትሎ አምስት ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር የኢንቨስትመንት ሥምምነት በማድረግ ፎረሙ በስኬት ተጠናቋል ነው ያሉት።
ይህም በ2015 በጀት ዓመት ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማምጣት ለተያዘው እቅድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው በመጠቆም።
ለኢንቨስትመንት ጥበቃ ማድረግና የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ መንግሥት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ፖሊሲዎችና የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና፣ ማዕድን፣ አይሲቲ፣ ቱሪዝምና ማኑፋክቸሪንግ ቁልፍ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሚሆኑ ገልጸው ባለሃብቶች እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢንቨስት ኢትዮጵያ ፎረም በየዓመቱ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጭ በተለያዩ ዘዴዎች የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።