ቀጥታ፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል የተሳታፊ ልየታ ስራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ)፦ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቀጥለው ሳምንት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል የተሳታፊ ልየታ ስራ በወረዳ ደረጃ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የኮሚሽኑን ቀጣይ ስራዎችና የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ስራዎችን በምእራፍ ከፋፍሎ እስካሁን ስኬታማ ሂደቶችን ማለፉን አስታውሰዋል።

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ለምክክር ሂደቱ ወሳኝ የሆነው የተሳታፊ ልየታ መካሄድ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

ሁሉንም አይነት የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል የልየታ ስራ እንደሚከናወን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በሂደቱ በእያንዳንዱ ወረዳ ዘጠኝ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደሚኖሩ ጠቅሰው እያንዳንዳቸው ሃምሳ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡ መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

እነዚህ አካላት በሚገባ ከተወያዩ በኋላ የውይይት ጽንሰ ሃሳብንና አጀንዳ አሰባሰብን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ከዘጠኙም ባለድርሻዎች ሁለት ሁለት ተወካዮች ተመርጠው ወደ ክልል የሚሄዱበት አሰራር መቀመጡንም አስረድተዋል።

በዚህም ከእያንዳንዱ ወረዳ የተወከሉ 18 ሰዎች ወደ ክልል በመሄድ ባመጧቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ የሚመረጡ አጀንዳዎችን ወደ ኮሚሽኑ የሚልኩ ይሆናል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በክልል ደረጃ ከተደራጁ የህብረተሰብ ተወካዮች ማለትም ከሰራተኛ ማህበራት፣ ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎችም አደረጃጀቶች አጀንዳዎች የሚሰበሰቡ ይሆናል ብለዋል፡፡

በፌደራል ደረጃም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎችን የማሰብሰብ ስራ በሂደት ይሰራል ብለዋል።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዜጎችም በሚዘረጋላቸው የመረጃ ግንኙነት አውታር አጀንዳ እንዲያቀርቡ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ በፌደራል ደረጃ አገራዊ የምክክር መድረክ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ኢትዮጵያውያን በዝርዝር እንዲመክሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የተቋቋመ በመሆኑ ለዚህ ዓላማ መሳካት ሁሉም ተሳትፎውን እንዲያጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም