የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተቋሙ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በተለይ አገልግሎትን ከማስፋትና ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ በልዩ ትኩረት መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የድርጅቱን የኦፕሬሽን አገልግሎት መጠን 4 ሚሊዮን 85 ሺህ 765 ቶን ለማድረስ ታቅዶ 4 ሚሊዮን 131 ሺህ 929 ቶን በማድረስ ከእቅዱ በላይ መፈፀሙን ገልጸዋል።
በጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት የድርጅቱን መርከቦች፣ የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም 2 ሚሊዮን 885 ሺህ በላይ ቶን በማጓጓዝ ከእቅድ በላይ ተከናውኗል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በተጠቀሰው ወራት በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት በኩል በመልቲሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት 66 ሺህ 194 ኮንቴይነር ለማጓጓዝ ታቅዶ 70 ሺህ 742 ኮንቴይነር በማጓጓዝ የተሳካ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
ለሀገር ልማት በተለይም ለግብርና ስራዎች ግብዓትን በማስገባት ረገድ የላቀ አፈፃፀም መታየቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የታገዘና ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ለማስፋት የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ ተቋሙ ግዙፍና ዘመናዊ የዳታ ማዕከል እያስገነባ መሆኑን ጠቅሰው በሰኔ ወር ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ይጀምራል ብለዋል።