ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ካላቸው ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ካላቸው አምስት የተለያዩ  አገራት ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።


ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ  እና የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን ከፈረሙት ውስጥ በሲሚንቶና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰማራውና 500 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል ያለው ሲኖማ የተሰኘው ኩባንያ አንዱ ነው።

በተጨማሪም በምግብ ማቀነባበሪያና ሌሎች ዘርፎች የሚሰማራውና 45 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል ያለው ኤ አይ ፉድ ኤንድ ዩኒሊቨር ማኑፍክቸሪንግ ሌላኛው ኩባንያ ነው።

በተመሳሳይ በእንጨት፣ ሎጅስቲክስና ሌሎች ዘርፎች 1 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል ስምምነት ያደረገው ሻንጉ ቲምበር ኤንድ ውድ አሶሲየሽን ኩባንያ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮ ቺክን ኤንድ ኤጂ ፒ በ30 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ቲያሸ በ80 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ካፒታል መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከኮሚሽኑ ጋረ ተፈራርመዋል።

የተደረጉ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ የሚኖረው ሲሆን ባለሀብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ተገልጿል።

ኩባንያዎቹ በስምምነቱ መሰረት ወደስራ ሲገቡ በኢትዮጵያ  የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና በስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም እንዲሁ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅን አልሞ ለሦስት ቀናት የተካሄደው "ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023" የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም