ቀጥታ፡

ጠንካራና ሰላሟ የፀና ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2015 (ኢዜአ)፡- ጠንካራና ሰላሟ የፀና ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም የሚውል የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል። 

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከንቲባዎች በትግራይ ክልል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተዋል።

በዚሁ መርሐግብር ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከንቲባዎችም ጦርነቱ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል በትግራይ ክልል ጉብኝት በማድረግ አብሮነትና አጋዥነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የጋራ ብልጽግና ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ሥራ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አረጋግጠዋል። 

የትግራይ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ በመቆም በአገር ሰላም፣ ልማትና እድገት ፅኑ መሰረት በማኖር ረገድ የጎላ ታሪክ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በጦርነቱ የደረሱ ውድመቶችን በጋራ መገንባትና እንደ አገር እድገትና ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣ ፈንታ እጅግ የተቆራኘና አገር በመገንባት ሂደት ላይ የሚያተኩር መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን የመገንባት አደራችንን በጋራ ልንወጣ ይገባል ሲሉም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል።

የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በተሟላ መልኩ የሚሳካው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ወንድማማችነቱን አጥብቆ በጋራ መሥራት ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል። 

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከንቲባዎች ጉብኝትም ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን የማፅናት ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ሂደት ኃላፊዎቹ ያሳዩትን ቁርጠኝነት በመጥቀስ የህዝቡ ትብብርና ድጋፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና አጋር አካላትም ለመልሶ ግንባታና የማቋቋም ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

በሁሉም መልኩ በመንግሥት የተጀመሩ የመልሶ ግንባታና የልማት ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አቶ አደም አረጋግጠዋል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ልዑኩ ትግራይ ክልል በመገኘት በጦርነቱ የተከሰተውን ጉዳት ጎብኝቶ  አጋርነቱን ስላረጋገጠ እናመሰግናለን ብለዋል። 

የሰላም ግንባታን አጠናክሮ ለመቀጠልና የመልሶ ግንባታን ለማፋጠን በአካል ተገኝተው በማየት አጋርነታቸውን በማሳየታቸው መልካም መሆኑን ገልጸዋል። 

 

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የሚሰራውን ሥራ በማገዝ ረገድ ጉብኝቱ ትልቅ እርምጃ ነው  ያሉት አቶ ጌታቸው የህዝብ ለህዝብ መቀራረብን ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል።

 

በብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት የአስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ሀሰን አብዱል ቃድር፤ የብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የበጦርነት የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አባላት እና አመራሩን በማስተባበረ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ማህበረሰቡን ወደ መደበኛ ህይወቱ በመመለስ ሂደት ፓርቲው የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ጠቁመው፤ የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ፓርቲው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች ሀገርን የመገንባት ግቡን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ያሉት ምባሳደር ሀሰን አብደል ቃድር፤ የትግራይ ክልል ህዝብም የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም