ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተሻለ መሠረት ላይ እያጸናች ነው--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተሻለ መሠረት ላይ እያጸናች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ አገሮች /ታንዛንያ፣ ኮሞሮስ፣ ቡሩንዲና ኡጋንዳ/ ያደረጉት ጉብኝት አፍሪካዊ ወዳጅነትን ለማጠናከር ማስቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አፍሪካ የኢትዮጵያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ትኩረት እና የዲፕሎማሲ መሠረት መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መሪ እና ለአፍሪካ ሀገሮች ነጻነት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገች ፣ ለአፍሪካ አንድነትና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታና መጠናከር መሪ ተዋናይ መሆኗንም አስታውሰዋል።

አፍሪካውያንም ኢትዮጵያ በፈለገቻቸው ወቅት በመርህ ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ሰጥተዋል ያሉት አቶ መለስ የአቶ ደመቀ መኮንን ጉብኝትም አፍሪካዉያን ወዳጆቻችንን የማጽናትና የማስፋት ዲፕሎማሲያዊ አካል ጥረት መሆኑን ተናግረዋል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብና የናይል ተፋሰስ አንፃር የበለጠ ለመደጋገፍ እና መግባባት ላይ እንዲደረስ ማስቻሉን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በኩል የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲቀጥል በጉብኝቱ ወቅት በተደረጉ ውይይቶች ከመግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።

አምባሳደር መለስ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተሳተፉበት ያለው የኢንቨስትመንት ጉባኤ አገሪቱ የሰላም ስምምነቱን እያጸናች ልዩ ትኩረት ወደ ምትሰጠው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ፊቷን እያዞረች ለመሆኗ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር መለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ዋና አዛዥ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጋር በስልክ መወያያታቸውን ገልፀዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ መሪዎች ልዩነቶቻቸውን በመግባባት እንዲፈቱ እና ለሀገራቸው መረጋጋትን ማምጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ብለዋል።

በሱዳን ለዜጎች ሊደረግ የሚችለው ድጋፍም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ያሉት አምባሳደር መለስ ሱዳን ካጋጠማት ወቅታዊ ፈተና እንድትወጣ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ከሱዳናዊያን ጎን መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መሪዎች ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ድረስ ሱዳን ያጋጠሟትን ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም