የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015 (ኢዜአ):- የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ፡፡

እኩልነትና ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሰባት ጠንካራ ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ አቶ ግርማ የተሰጣቸውን ታላቅ ሕዝባዊ ድርጅታዊና መንግስታዊ ኃላፊነት በልበ ሙሉነት፣ በትጋትና በኃላፊነት ስሜት የተወጡ ናቸው ብሏል ምክር ቤቱ፡፡

አቶ ግርማ የሺጥላ ሀገር ወዳድ ብልኅ እና ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር እንደነበሩ ገልጾ ለሀገርና ለወገን ሲሉ ሙሉ ጊዜያቸውን በመጨረሻም የማይተካውን ውድ ሕይወታቸውን ሰውተዋል ብሏል፡፡

የአቶ ግርማ ጉልኅ ሀገራዊና መንግስታዊ አበርክቶ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ማኅደር ፈፅሞ የሚዘነጋ አይሆንም ነው ያለው ምክር ቤቱ በሐዘን መግለጫው፡፡

ምክር ቤቱ በአቶ ግርማ የሺጥላና በግል ጠባቂዎቻቸው ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ለወገኖቻችን ሞት ምክንያት የሆነውንም አሳፋሪ ፅንፈኛ ድርጊትና ጥቃት በፅኑ በማውገዝ ለቤተሰቦቻቸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለስራ ባልደረቦቻቸው መፅናናትን መመኘቱን ከምክር ቤቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም