ቀጥታ፡

በምሥራቅ ባሌ ዞን የወጣቶች አደረጃጀት የሚሳተፍበት የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ንቅናቄ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

ጎባ፣ ሚያዝያ 20/2015 (ኢዜአ). በምሥራቅ ባሌ ዞን የወጣቶች አደረጃጀት የሚሳተፍበት የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

በዞኑ እየተካሄደ የሚገኘው የንቅናቄ መድረክ "እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ቃል መሆኑ ተመላክቷል። 

ወጣቶች የሚሳተፉበት ይኸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭና ድጋፍ መርሃ ግብር ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገልጿል። 

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወጣት አህመድኑር አልይ እንዳሉት፣ የዞኑ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ግንባታ በገንዘብና በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። 

ለአንድ ወር በሚቆየው የንቅናቄ መርሐ ግብርም ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከቦንድ ሽያጭ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን አክለዋል። 

ኃላፊው እንዳሉት፣ የንቅናቄ መድረኩ ወጣቶች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከማሳደግም በላይ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። 

ንቅናቄው በተጀመረ ጥቂት ቀናት በወጣቶች በተደረገ ተሳትፎ 400 ሺህ ብር የሚጠጋ የቦንድ ግዥ መፈጸሙን ጠቅሰዋል። 

በንቅናቄው ከቦንድ ሽያጭ ባለፈ የተለያዩ የስፖርታዊና የኪነጥበብ ውድድሮች ጨምሮ ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን በመጠቀም ዕቅዱን ለማሳካት ይሰራል ነው ያሉት። 

የዞኑ ወጣቶችም ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ እንዲረባረቡ ጠይቋል። 

ከዞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት  አቶ አሰፋ መኮንን  የዞኑ ህዝብ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስፈጸሚያ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በሀሳብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል። 

በወጣቶች የንቅናቄ መድረክ ለማሰባሰብ የታቀደው 9 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆነ ነው የገለጹት። 

በቦንድ ግዥው ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት አደም ሁሴን በሰጠው አስተያየት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ ታስቦ የሚሰራ የትውልድ ፕሮጀክት በመሆኑ የ2 ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን ተናግሯል። 

የአንድ ሺህ ብር ቦንድ ግዥ የፈጸመው ሌላው ወጣት መንግስቱ አለሙ በበኩሉ፣ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ መግዛት በግድቡ ግንባታ ላይ አሻራን ከማሳረፍ በተጨማሪ ለቁጠባም ጥሩ መሆኑን ተናግሯል። 

ወጣቶቹ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት። 

በምሥራቅ ባሌ ዞን እስካሁን የቦንድ ግዥን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ለግድቡ ግንባታ መዋጣቱን የዞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ  ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም