ቀጥታ፡

የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰሩ ሃይሎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰሩ ሃይሎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የተቋሙን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በምክር ቤቱ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።

የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄና አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

የሀገርን ሀብትና ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል በተለያዩ አካላት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በመከላከልና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ጥሩ ውጤት እየታየበት መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ረገድም እንዲሁ።


 

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ፤ ፌዴራል ፖሊስ የተለያዩ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።

በቀጣይም የወንጀል መከላከል ስራን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የማከናወን ስራ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ ስራዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ የሄደበት ርቀት  የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን መከላከል ላይ በቀጣይ ዋነኛ ትኩረቱ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በተለይም የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰሩ ሃይሎችን የመከላከልና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ተቋሙ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ወንጀሎችን የመከላከልና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ተግባሩን ቀጥሏል ብለዋል። 


 

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ የነበሩ ከ2 ሺህ 3 በላይ ሰዎች እንዲመለሱ መደረጉንና በወንጀሉ የተሳተፉ 63 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ጠቅሰዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የውጭ አገር ገንዘብ ከወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙንም እንዲሁ።

በመሆኑም በቀጣይ የወንጀል መከላከል ስራዎችንና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም በጥሩ ጅምር ላይ ያሉ ስራዎችን በማጠናከር የአገር ህልውናን የማስጠበቅና ወንጀለኞችን በህግ አግባብ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም