ቀጥታ፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ባህር ዳር ከተማና ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2015(ኢዜአ):- በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ በባህር ዳር ከተማና ኢትዮጵያ መድን መካከል ይደረጋል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ባህር ዳር ከተማ በ42 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

ባህር ዳር በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፏል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል።አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ጨዋታው ባህር ዳር ከተማ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ልዩነት ወደ ሶስት ለማውረድ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን ከዋንጫው ፉክክር ላለመራቅ የሚያደርጉት በመሆኑ ብርቱ የሆነ ፉክክር ይጠበቃል።

የሁለቱን ክለቦች ተጠባቂ  ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 3 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።

በሌላኛው የሊጉ የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ 27 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ስምንተኛና ዘጠነኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስቱ የሊጉ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የ21ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐግብር ከዛሬ ጨዋታዎች በኋላ ይጠናቀቃል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ21ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ መቻልን 1 ለ 0 ሲረታ ወልቂጤ ከተማና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት እኩል ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም