ቀጥታ፡

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015(ኢዜአ)፦የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ገለጸ።

ክልሉ ባወጣው መግለጫ የሠላም ምህዳሩ ሰፍቶ ነገሮች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ እያገኙ ባለበት በዚህ የብርሃን ወቅት፣ ወደኋላ በመመለስ ጨለማን በመምረጥ በውይይትና በንግግር፣ ሃሳብን በሀሳብ ማሸነፍ እየተቻለ እንደዚህ ያለ እኩይ ተግባርን መፈፀም የተሸናፊዎች ስነ-ልቦና መገለጫ ነው ብሏል።

አቶ ግርማ የሺጥላ ባለ ብሩህ አእምሮ እና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ሀሳቦችን የሚያመነጭ፣ በተግባርም የሚገልፅ፣ ወደ ፊትም በርካታ አበርክቶዎችን ለሀገሩ ያበረክታል ተብሎ የሚጠበቅ ውድ የሀገር ልጅ የነበረ ቢሆንም እኩይ አላማን ባነገቡ አካላት ህይወቱ ሊቀጠፍ በመቻሉ ከልብ ሀዘን ተሰምቶናል ብሏል።

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለአቶ ግርማ የሺጥላ ቤተሰቦች፣ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው የአማራ ክልል ህዝብ መፅናናትን ይመኛል ማለቱን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም