የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015(ኢዜአ)፦የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ሃዘን ገለጸ።
የመነግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፦
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ግርማ የሺጥላ በጽንፈኛ ኃይሎች መገደላቸውን ሲሰማ የተሠማን ሀዘን ጥልቅ ነው።
የክልሉ መንግሥት ባወጣው የሀዘን መግለጫ ሀገራችን ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በተጋች ቁጥር ዘመን ያለፈበትን የጽንፈኝነት መንገድን መርጠው የሕዝብ ልጅ በሆነው ግርማ የሺጥላ ልብ ሠባሪ ጥቃት በፈጽሙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል።
የእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች ዓላማ ሀገር የማፍረስ እና ግልጽ ሽብር በመፍጠር የህዝቦች አብሮነት እንዲሸረሸር የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም አምርሮ ሊታገላቸው እንደሚገባ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትም በግርማ የሺጥላ ላይ የተፈጸመውን ግድያ እያወገዘ፣ የሀሳብ ሜዳ በሠፋበት በዚህ ወቅት ጽንፈኝነት የመረጡ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ ያረጋግጣል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በዛሬው ዕለት በአቶ ግርማ የሺጥላ በደረሰው ድንገተኛ እና ልብ ሰባሪ ጥቃት የተሠማውን መሪር ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውና እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት
ሚያዚያ 19/2015 ዓ.ም
አሶሳ፣