ቀጥታ፡

በድርቅና የጎርፍ አደጋ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል -የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፡ በድርቅና የጎርፍ አደጋ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅና በጎርፍ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና መልሶ የማቋቋም ስራ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ባካሔደው የቁጥጥር ስራ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የቁጥጥር ስራው የተቋማት ኃላፊዎችና ነዋሪዎች የክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤቶች፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ክልል ''ቡሳ ጎኖፋ''፣ የዞኖችና የወረዳዎች ላይ መካሄዱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በየደረጃው የሚገኙ ለአደጋ መከላከል የተቋቋሙ ግብረ ኃይሎች በድርቅና በጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለው ከሚገኙ ወገኖች ጋር ውይይት በማድረግ መረጃዎቹ መደራጀታቸውን ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የዋናው መስሪያ ቤት የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ፣  ተቋሙ  ለረዥም ቀናት የቁጥጥር ስራውን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም፣ በኦሮሚያ  ቦረና ዞን፣ በሶማሌ  ዳዋ ዞኖች፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በተመረጡ አስር ወረዳዎችና በመጠለያ ጣቢያዎች ከመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም የቁጥጥር ስራው ተሰርቷል ብለዋል።

በሂደቱም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ድርቁን ለመቋቋም ከመጠባበቂያ በጀት ላይ በመመደብ እና ሕዝቡን በማሳተፍ ያከናወናቸው ስራዎች በጠንካራ ጎን ተነስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በቡሳ ጎኖፋ አደረጃጀት ለአደጋ ጊዜና ለሚከሰቱ የተፈጥሮ ችግሮች የሚውል በህዝብ ተሳትፎ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና እህል ማሰባሰቡን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በዞኑ በዝናብ እጥረት ሳቢያ በተከታታይ አመታት ድርቅ የተከሰተ ሲሆን በዘርፉ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን ተቀብሎ የቅድመ መከላከል ስራ ለመስራት ያለመቻሉ በክፍተት የሚታይ ሆኗል ነው ያሉት።

በድርቅ ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ሁሉም ቦታ ተደራሽ በማድረግና ፍትሃዊ የሆነ ስርጭት እንዲኖር በየደረጃው ጠንካራ ክትትል ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች መሆኖራቸውንም አንስተዋል።

በሶማሌ ክልል በተመሳሳይ ማህበረሰቡ የቆየውን የመተጋገዝ ባህል በማዳበር በመረዳዳትና የዞኑ መስተዳደር ባደረገው ጥረት ድርቁን በመቋቋም ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑ ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም በክልሉ በድርቅ ሳቢያ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች  የሚገኙ ዜጎች ለሚደረግላቸው ሰብዓዊ ድጋፍና እርዳታ እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ያለመሆኑ እንደ ክፍተት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞንም እንዲሁ ለረዥም ዓመታት ድርቁ የቀጠለ ቢሆንም ለእንስሳትና ለማሕበረሰቡ የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ድርቁን ለመቋቋም የተደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን በዞኑ ወጥ በሆነና በተደራጀ መልኩ የተጎጂዎችና ተፈናቃዮችን መረጃ በጾታ፣ በአባወራ፣ በእድሜና በአካል ጉዳተኞች ተለይቶ ያለመደራጀቱ እንደ ክፍተት የሚታይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም በግኝቱ መንግስትና ህዝብ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሎቹ መስተዳድርና ምክር ቤቶችም በድርቅና ጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተቋማት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም