የጋምቤላ ክልል መንግስት በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ኃዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል መንግስት በአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ኃዘን ገለጸ
ጋምቤላ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልል መንግስት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ኃዘን ገልጿል።
ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠው የሃዘን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈፀመው ግድያ በእጅጉ ያሳዝናል።
ለህልፈተ ሕይወት የተዳረጉት ከፍተኛ አመራር ለሀገሪቱ የላቀ አገልግሎት የሰጡ መሆናቸውን ጠቅሶ በአመራርነት ዘመናቸው በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን ያገለገሉ መሪ እንደነበሩም አመልክቷል።
በተፈጸመው ድርጊት የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእጅጉ ማዘኑንና ድርጊቱንም እንደሚያውግዝ አስታውቋል።
በሕይወት ላጣናቸው ከፍተኛ አመራር ሞት የክልሉ መንግስት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ ፤ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
ግድያው የክልሉ መንግስት ለህዝቦች የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የጀመረውን ሁለተናዊ ለውጥ ፈጽሞ እንደማያደናቅፈውም በመግለጫው አመላክቷል።
ሀገራዊ ለውጡ እንደማይደናቀፍና መላው ህዝብም መስዋዕትነት የተከፈለበትን ለውጥ ከዳር ሊያደርሰው እንደሚገባ በመግለጫው ጠቅሷል።