የጽንፈኝነትን ሰይጣናዊነት ያሳየ የግፍ ግድያ-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የጽንፈኝነትን ሰይጣናዊነት ያሳየ የግፍ ግድያ-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጽንፈኝነት ብዙዎችን የሕዝብ ልጆች አሳጥቶናል። ጽንፈኞች ሰው መሆንን ይጠየፋሉ።
ዛሬ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ግርማ የሺ ጥላ ባደገበት ቀየ በጽንፈኞች በግፍ ተገድሏል። ይህም የጽንፈኛው ኃይል የመርዝ ፖለቲካ በቀየ የማይወሰን፣ ከጓዳ ጭምር ገብቶ ቤተሰብን የሚበትን መሆኑን አሳይቶናል።
ውዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ!
አጀንዳ አልባ የጥላቻ ፖለቲካ ዘርተው ጽንፈኝነትን በማብቀል ልጆችህን በየአደባባዩ የሚቀጥፉ የደም ነጋዴዎችን ማስቆም ካልቻልክ፣ የግፍ በትራቸውን የብዙኃኑን ቤት ማንኳኳቱ አይቀሬ ነው።
ዓላማቸው ማተራመስና ሀገራችንን ዕረፍት መንሣት የሆኑ አካላት አሉ። የእነዚህ አካላት አርአያዎቻቸው ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ናቸው። የእነርሱን ተግባር በኢትዮጵያ ለመድገምና ኢትዮጵያን ለማጥፋት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያልተፈጸሙ ዘግናኝ ተግባራትን ሁሉ ይፈጽማሉ።
ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማበልጸግ የጀመርነውን ትግል ጽንፈኞች አያስቆሙትም። ይሄንን ነውረኛ ዘግናኝ ተግባር የፈጸሙት የትም ቢገቡ ለሕግ ይቀርባሉ። ሌሎች በእነርሱ መንገድ መጓዝ የጀመሩ በሕግ ማስከበር እንዲቆሙ ይደረጋል።
ነብስህ በሰላም ትረፍ!
ሚያዝያ19 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ