የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአይ.ሲ.ቲ ዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአይ.ሲ.ቲ ዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015 (ኢዜአ) የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ማምረቻው ዘርፍ ባሉ ምቹ ሁኔታዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለኃብቶች የሚያስተዋውቅ "ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ" የተሰኘ መድረክ አዘጋጅቷል።
በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም መንግስት የአይ.ሲ.ቲና በዘርፉ በማምረቻ መስኮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አራት ዘርፎች አንዱ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ በተጀመረው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" በዋናነት የአይ ሲ ቲ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ ተደራሽነትን ማረጋገጥና በዘርፉ ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ ቅድሚያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የተለያዩ መደላድሎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም የፋይናንስ ተደራሽነትንና የሳይበር ደህንነትን እውን ለማድረግ በዘርፉ ከሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ እንደነበር በማስታወስ አሁን ላይ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በርካታ ማበረታቻዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ቴሬሳ በበኩላቸው መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ያቋቋማቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለኢንቨስትመንት መጎልበት ምቹ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መንግስትና ባለሃብቶች በተመረጡ አካባቢዎች የገነቧቸው 29 የኢንዱስትሪ ፓርኮች 250 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፓርኮቹ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
አሁን ላይ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገቡ የሚገኙ የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ደረጃ በእጅጉ መሻሻላቸውን በመጥቀስ ሁሉም ለምርት ተግባር ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ በርካታ ባለሃብቶች የማምረቻ መሳሪያ በመግጠምና በምርት ሂደት ላይ መገኘታቸው የዚህ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉና ዘመናዊ ሼዶች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ፎረሙ ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የመጡ ከ600 በላይ ባለሃብቶች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡