የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/ 2015 (ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሃዘን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ብሩህ ራዕይ በሀሳብ ድሆች አይሞትም!
የፖለቲካ አመለካከትን በዕውቀትና በእውነት ማራመድ የተሳናቸው የሀሳብ ድሆች ማሰብ የሚችሉ ባለ ብሩህ ራዕይ ሰዎችን ማጥቃት ብቸኛ አማራጫቸው ነው።
ግርማ የሺጥላ የኢትዮጵያውያንን ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለማጽናት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ቀን ከለሊት ሲሰራ የነበረ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ ነበር።
ሀሳብ የነጠፈባቸው ጽንፈኛ ብሔርተኞች ሰላማዊውን የሀሳብ መድረክ መቋቋም እንደማይችሉ ስለሚያውቁ ኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ዕድሜውን ሙሉ የለፋውን ብርቱ መሪ በልተውታል።
ወንድማችን ግርማ በሙሉ አቅሙ የታገለው ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔሮች፣ ሀይማኖቶችና ሌሎች ማንነቶች እኩልነትና ለዜጎች ነጻነት ነበር።
ይህ ያልተዋጠላቸው የሀሳብ ቆሞ ቀሮች ብሩ ሀሳብን በጥይት መግደል የሚቻል መስሏቸው ተራማጅ ሀሳብ የነበረውን ባለ ጽኑ አቋም መሪ ህይወት ቀጥፈዋል።
ይህን አስነዋሪ የወንጀል ድርጊት በፈጸሙ ጽንፈኛ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በሀሳብ የበላይነት እያመከንን በኢትዮጵያዊያን መካከል አስተማማኝ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ የህዝቦችን እኩልነት፣ ነጻነትና ወንድማማችነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው የህዝቦች ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ወንድማችን ግርማ ነፍስህ በሰላም ትረፍ!